ኢትዮጵያ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ76,000 በላይ ስደተኞችን ተቀብላለች ሲል የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 08/01/2018፡- ኢትዮጵያ በሱዳን እየተካሄደ የሚገኘውን ግጭት በመሸሽ ከቀያቸው የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን መቀበሏን ቀጥላለች ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ።
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ስደተኞች መካከልም የሱዳን ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ከለላን የሚሹ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል ብሏል።
ኮሚሽኑ “ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው የስደተኞች እንቅስቃሴ” በሚል ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርቱ በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ እስከ ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በድምሩ 76,052 ዓለም አቀፍ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጿል።
ሪፖርቱ አክሎም፣ በ2017 ዓ.ም ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 8,268 መድረሱን ጠቁሟል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ገብተዋል ከተባሉ 76,052 ስደተኞች መሀከልም 45,118 ሱዳናውያን ሲሆኑ፣ 20,226 ኢትዮጵያውያን፣ 8,284 ኤርትራውያን እና 2,424 የሚሆኑት ደግሞ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ናቸው ተብሏል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት (RRS) ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ባሉ የመግቢያ ቦታዎች ላይ አዲስ የሚገቡ ስደተኞችን የማጣራትና የመመዝገብ ሥራ መቀጠሉም ተመላክቷል።