ቡርኪናፋሶ ለሁሉም አፍሪካውያን ተጓዦች ከቪዛ ነፃ ጉዞን ፈቀደች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/01/2017፡- ቡርኪናፋሶ ሰዎችን እና ሸቀጦችን ወደ ሀገሪቱ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲሁም ሀገሪቱ ያላትን ቀጠናዊ ትስስር ለማጠናከር በማሰብ ለሁሉም አፍሪካውያን ተጓዦች ከቪዛ ነፃ ጉዞ መፍቀዷን አስታውቃለች፡፡
በወታደራዊ መንግሥት መሪው ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ የተመራው ካቢኔ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ የሀገሪቱ የደህንነት ሚኒስትር ማሃማዱ ሳና፤ “ከአሁን ጀምሮ ወደ ቡርኪናፋሶ መሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ምንም አይነት ክፍያ አይከፍልም” ብለዋል።
“ሆኖም አፍሪካውያን ጎብኝዎች የኦንላይን ቪዛ ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ፣ ይህም እንዲፀድቅ ይገመገማል” ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በዚህም ሀገሪቱ እንደ ጋና፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ያሉ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን በመቀላቀል ለአፍሪካውያን ጎብኝዎች የጉዞ መስፈርቶችን መቃለሏን ቢቢሲ ዘግቧል።
እ.ኤ.አ በ2022 መፈንቅለ መንግሥት ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ወጣቱ የወታደራዊ መንግሥት መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ እራሳቸውን የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ አድርገው የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ይህም ብዙ ጊዜ ምዕራባውያን ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል፡፡
‘ለአህጉሪቱ ዜጎች የቪዛ ክፍያዎች መሰረዙ ቡርኪናፋሶ ከፓን አፍሪካኒዝም ሀሳቦች ጋር ያላትን ትስስር የሚያንፀባርቅ እና ክልላዊ ውህደትን የሚያበረታታ’ መሆኑን የወታደራዊ መንግሥቱ የመረጃ አገልግሎት ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ተናግሯል።
“ይህ ለአፍሪካውያን ዜጎች የነጻ ቪዛ ስርዓት ቱሪዝምን እና የቡርኪናፋሶን ባህልን በማስተዋወቅ ሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ትኩረትን እንድትስብ ይረዳል” ሲል በመግለጫው አክሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የአህጉሪቱ ጎብኚዎች ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ያጋጥማቸው የነቡትን የጉዞ መስፈርቶች ለማቃለል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ይህም በአህጉሪቱ ውስጥ ጉዞን ለማመቻቸት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ አግኝቷል።
እ.ኤ.አ በ2025 መጀመሪያ ላይ ጋና ሁሉም ፓስፖርት የያዙ የአፍሪካ ሀገራት ጎብኚዎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደሀገሪቱ መግባት እንደሚችሉ ማስታወቋ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ኬንያ ከሶማሊያ እና ከሊቢያ በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እና የተወሰኑ የካረቢያን ሀገራት ዜጎች ከኤሌክትሮኒክ የጉዞ ፍቃድ ነፃ እንዲሆኑ የሚያስችል ፖሊሲ ያስተዋወቀች ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሩዋንዳም አፍሪካውያን ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቷ ለመግባት ቪዛ እንደማያስፈልጋቸው አስታውቃለች።
የቡርኪናፋሶ ይህ አዲስ እርምጃ በመውሰድ እነዚህን ሀገራት መቀላቀሏ፤ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ይረዳታል ተብሎም ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ቡርኪናፋሶ፣ በወታደራዊ መንግሥት ከሚመሩ ማሊ እና ኒጀር ጋር ህብረት በመፍጠር የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ለቀው መውጣታቸውን ይታወሳል፡፡