አፍሪካኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የውስጣዊ ችግሮች ለመሸፈን የተፈበረከ አጀንዳ ነው ስትል ኤርትራ ገለፀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/01/2017፡- የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ትላንት በመስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ባወጣው ትንታኔ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ “ሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት” በሚል ይፋ ያደረገውን እንቅስቃሴ አጥብቆ አውግዟል።

ትንታኔው ይህንን አጀንዳ “ከእውነት የራቀ፣ አደገኛ እና ህገ-ወጥ” ሲል የፈረጀው ሲሆን፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት በተለያዩ የሚዲያ ዘመቻዎችና ስነ-ስርዓቶች ጉዳዩን ህጋዊ ለማስመሰል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ሲል ይከሳል።

በኤርትራ እይታ፣ ይህ የባህር በር ጥያቄ የኢትዮጵያን ከባድ ውስጣዊ ችግሮች ለመሸፈን ታስቦ የተነሳ የፖለቲካ ማዘናጊያ ስልት ነው።

መንግስት በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የሚታመሰውን ኢኮኖሚና በመላ አገሪቱ የተስፋፉትን የውስጥ ግጭቶች ከመፍታት ይልቅ፣ ህዝባዊ ትኩረትን ወደ ውጫዊ ጉዳይ በማዞር ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሞከረ ነው ሲል ትንታኔው ይሞግታል።

ከዚህም ባሻገር ጽሑፉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ታሪክን እያዛቡና ያለፈውን የኃይል ውህደት (annexation) ዘመን በማወደስ የሉዓላዊነት መርህን እየጣሱ ነው ሲል ይከሳል። ይህ ድርጊት የኤርትራን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጋፋ ብቻ ሳይሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ቻርተርንና የአፍሪካ ህብረት መስራች ህግን ጨምሮ መሰረታዊ የሆኑ አለም አቀፍ ህጎችን የሚጻረር መሆኑን ያስረዳል።

በሌላ በኩል ጽሑፉ ኤርትራ ከጎረቤቶቿ ጋር መተባበርን እንደማትቃወም ያሰምርበታል። ይሁንና ማንኛውም ትብብር በአንድ ወገን ጀብደኝነት ላይ ሳይሆን በጋራ መከባበር፣ በህጋዊ ግልጽነትና ለቀጠናው ሰላም በጋራ በመቆም ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል።

ትንታኔው፣ በማጠቃለያውም፣ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ መሪዎች ይህንን “አደገኛ ቅዠት” በመተው፣ ትኩረታቸውን የሀገር ውስጥ ሰላምን ወደማስፈንና የተጎዳውን ኢኮኖሚ ወደማደስ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል። ይህን ማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቀጠናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ትንታኔው ያመለክታል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates