አፍሪካኢትዮጵያ

የህዳሴ ግድብ የህልውናችን ስጋት ነው አሉ ግብፅና ሱዳን።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/12/2017፡- ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው እና ሊመረቅ ቀናት የቀሩት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል አሉ።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ አጠናቅቃ ለምረቃ እየተዘጋጀች ባለችብት ጊዜ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች በካይሮ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነው ስጋታቸውን የገለጹት።

በሚኒስትሮቹ ረቡዕ ነሐሴ 28/ 2017 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ ግድቡ “በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ መረጋጋት ላይ ቀጣይነት ያለው ስጋት” መደቀኑን አመልክተዋል።
የሁለቱ አገራት ሚኒስትሮች በካይሮ ባደረጉት በዚህ ስብሰባ ላይ ግድቡ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እና በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ ለመሙላት የወሰደችው የተናጠል እርምጃ የተቃወሙት አገራቱ የውሃ ደኅንነታቸው ጉዳይ አንድ እና የማይነጣጠል መሆኑን በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

አክለውም “ኢትዮጵያ ትብብርን ዳግም ለማጠናከር በምሥራቃዊ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ መቀየር አለባት” ብለዋል።

ግብፅ እና ሱዳን በዚህ መግለጫቸው ሌሎች የናይል ተፋሰስ አገራትን ተሳትፎ ውድቅ አድርገው ጉዳዩ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና ሱዳን መካከል ብቻ መታየት እንዳለበት አስታውቀዋል።

በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ በሦስቱ አገራት መካከል የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ እየተካሄዱ የነበሩ ድርድሮች ውጤት ሳያመጡ ተቋርጠዋል።

የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር አሁንም ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates