የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እመርታ በወታደራዊ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/12/2017፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኤሮ ዓባይ የድሮን ማምረቻን የሥራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት አንድን ሀገር ከሚያቆሟት ምሰሶዎች መካከል አንደኛው የኢኮኖሚ ለውጥ ነው ፡፡
አሁን በተጀመረው ሪፎርም የወጪ ንግድም ሆነ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ፤ ከተሞች እየዘመኑና ፕሮጀክቶችም በጥራትና በፍጥነት እየተጠናቀቁ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እመርታ ከሚያሳዩ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ተርታ አንዷ እንደሆነችም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለሀገር ብልጽግና የሚያስቡ ሰዎች ስብስብ በቀጣይ ሊያስቡት የሚገባው ጉዳይም ወታደራዊ አቅምን ማጠናከር መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በኢኮኖሚ እድገትና ወታደራዊ አቅም በቅደም ተከተል አብረው ማደግ ካልቻሉ ኢኮኖሚው በአቅም ማነስ ምክንያት ተመልሶ ሊበላ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና የማያጠራጥር ሐቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በኢኮኖሚ የተጀመሩ ሥራዎችን በወታደራዊ አቅም ማጠናከርና መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለት ጠቅሰው÷ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
ይህ ሁለንተናዊ እድገትም በወታደራዊ አቅም መጠናከር አለበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
አሁን ላይ አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖችን በስፋት እያመረትን እንገኛለን ፤ እነዚህም የጠላትን ስብስብ ለማጥፋት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያመረተቻቸው የሚገኙ ድሮኖች የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ እንደሚያስችሉም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂዎችን ከመግዛት አልፋ ማምረት መጀመሯ በዘርፉ አስደናቂና ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡