የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች እንደሚከበሩ መንግስት አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/12/2017፡- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች በመላው ሀገሪቱ ይከበራሉ ብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ዓመታት የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበሩ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮም የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች እና በልዩ ልዩ ዝግቶች በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበሩ አብራርተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የተገኘውን ህልም እና ትልም ለማህበረሰቡ በማስገንዘብ ለመጪው አዲስ ዓመት ግብዓት ለማድረግ በልዩ ስያሜ ቀናቶቹ እንደሚከበሩ ገልጸዋል፡፡
የ2017 ዓ.ም የጳጉሜን ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች እና መሪ ቃል እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፤ በዚህም ጳጉሜን 1 የፅናት ቀን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ‘ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል ብለዋል፡፡
ጳጉሜን 2 የህብር ቀን በሚል ስያሜ የሚከበር ሲሆን ‘ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ’ በሚል መሪ ቃል ተከብሮ እንደሚውል አብራርቷል፡፡
ጳጉሜን 3 የእምርታ ቀን የሚል ስያሜ የያዘ ሲሆን ‘እምርታ ለዘላቂ ከፍታ’ በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን በሚል ስያሜ የሚከበር ሲሆን ‘ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል ብለዋል፡፡
ጳጉሜን 5 የነገው ቀን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ‘ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ’ በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር አብራርተዋል፡፡
የዘንድሮ የጳጉሜን ቀናት በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ስያሜዎች ሲከበሩ ስኬቶችን በማጉላት ድክመቶችን ለማረም በመዘጋጀት የመሻገሪያ መንገዶችን በመተለም ነው ብለዋል፡፡