
ኢትዮ ሞኒተር፡ 08/12/2017፡ በአፋር ክልል ልዩ ሥሙ ሌዲ ገራሩ በተባለ የፓሊዮአንትሮፖሎጂ የጥናት ስፍራ፤ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያለው የሰው ልጅን አመጣጥ አስረጂ የሆነ አዲስ የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ እና የሆሞ ቅሪተ አካላት መገኘቱ ተገልጿል።
የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ የሳይንቲስቶች እና የተመራማሪዎች ቡድን ባደረጉት ምርምር የሰው ቅሪተ አካሉን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ግኝቱን ለማብሰር በቅርስ ባለስልጣን አዳራሽ በትናንትናው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባው አያሌው፤ “ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ይበልጥ የሚያጠናክርና በዘርፉ ያላትን ቀደምትነት የሚያረጋግጥ ውጤት ነው” ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ጥናቶች ሲያከናውን መቆየቱንና በቀጣይም ተጨማሪ ጥናቶችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡
የጥናት ቡድኑ በአካባቢው ባደረገው ምርምር 13 ጥርሶችን ያገኘ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ ቅሪተ አካል የተገኘበት አካባቢ ላይ ቅሪተ አካሉ መገኘቱ ተመላክቷል።
ግኝቱ በታዋቂው የሳይንስና ምርምር መፅሔት ኔቸር (Nature) ላይ የታተመም ሲሆን፤ ቅሪተ አካሉ ተጨማሪ ምርምሮች ተደርጎበት ስያሜ እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡