ጤና
አዲስ አበባ በዓለም ላይ “ከፍተኛ” የአየር ብክለት ካለባቸው ከተሞች ውስጥ አንዷ ሆነች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/12/2017፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የአየር ብክለት መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የስዊዘርላንድ የአየር ጥራት ተቋም የሆነው IQAir አስታውቋል።
ድርጅቱ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት በዓለም ላይ ከፍተኛ የአየር ብክለት ካለባቸው ከተሞች መካካል አዲስ አበባ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ገልጿል።
የከተማዋ የአየር ሁኔታ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ገደብ በከፍተኛ ደረጃ ማለፉን የገለጸው ሪፖርቱ፤ “ጤናማ ያልሆነ” በሚል ምድብ ውስጥ መካተቷን አመላክቷል።
በዕለቱ በተደረገው ምዘና፣ የአዲስ አበባ የአየር ጥራት መረጃ ጠቋሚ (AQI) 147 ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በተለይ እንደ የመተንፈሻ አካላት ችግር ወይም የልብ ህመም ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና ስጋት መሆኑ ተጠቁሟል።
ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ ጭስ፣ በባዮማስ ማቃጠል፣ ከግንባታ እና ከጠጠር መንገዶች የሚነሳ አቧራ እንዲሁም ቆሻሻን ማቃጠል የከተማዋ የአየር ብክለት ዋነኛ መንሰኤዎች ናቸው ተብሏል።
በሪፖርቱ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ በአየር ብክለት እስከ ዛሬ ባለው ሪፖርት ቀዳሚውን ደረጃ የያዘች ሲሆን አዲስ አበባ በዛሬው ዕለት ከ 4ኛ ደረጃ ወደ 26 ዝቅ ብላለች።