በየመን የባህር ዳርቻ የስደተኞች ጀልባ ተገልብጣ 68 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ማለፉ ተገለፀ።
በጀልባው ሲጓዙ የነበሩት 154 ስደተኞች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ እየተነገረ ነው።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 28/11/2017፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (IOM) ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በየመን የባህር ላይ ሰጥማ 68 ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉን አስታወቋል።
ትናንት እሁድ ማለዳ ላይ ከሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ከነበሩት 154 ስደተኞች መካከል 68ቱ ሲሞቱ፣ 74 የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን ያሉበት አለመታወቁን የተመድ የስደተኞች ድርጅትን ጠቅሶ አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
“በጀልባዋ ላይ የነበሩት ተሳፋሪዎች በሙሉ የኢትዮጵያ ዜጎች እንደነበሩ” የተገለጸ ሲሆን በየመን አብያን ግዛት የባህር ዳርቻ ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ አስከሬኖች መገኘቱ በዘገባው ተመላክቷል።
በየተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ተወካይ የሆኑት አቤዱሳቶር ኢሶቭ በበኩላቸው ‘ካንፋር ‘ በተባለ አካባቢ የ54 ስደተኞች አስክሬን በውቅያኖስ ዳር የተለያየ ቦታ ወድቆ መገኘቱን በሌላ ቦታ የተገኘ 14 አስክሬን ወደ ሆስፒታል መላኩን ተናግረዋል።
12 ሰዎች ደግሞ በህይወት መትረፋቸው የተገለጸ ሲሆን የአከባቢው ባለስልጣናት በአሁኑ ወቅት በአሰሳ እና የማዳን ስራ ላይ መሰማራታቸው ተመላክቷል።
ጀልባዋ ስደተኞቹን ይዛ ስትጓዝ የነበረው ወደ የመን ሲሆን ሀገሪቱ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ባሉ የባህረ ሰላጤው አገሮች ለመድረስ ለሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ መሸጋገሪያ ነች። የተመድ የስደተኞች ድርጅት እንዳስታወቀው፣ የመን በእርስ በርስ ጦርነት ብትታመስም የአፍሪካ ስደተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያስተናገደች ትገኛለች።