”በእስራኤል ጄኖሳይድ ተፈጽመዋል”

ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/11/2017፡ ሁለት የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “እስራኤል በጋዛ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው” ሲሉ አስታወቁ።
በእስራኤል የሚገኙ ሁለት አንጋፋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሆኑት በትሴለም እና ‘ፒዚሽያንስ ፎር ሂውማን ራይትስ’ እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ “የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ነው” ሲሉ ባደረጉት ጥናት ይፋ አድርጓል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ትላንት ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጡት ሪፖርት እስራኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት መካከል በጋዛ የሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ፍልስጤማዊ በመሆናቸው ብቻ የጥቃት ኢላማ አድርጋቸዋለች ሲሉ ከሰዋል።
በዚህም በፍልስጤማውያን ላይ ከፍተኛ እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም የማይጠገን ጉዳት ደርሷል ያሉት የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ፤ አያይዘውም የእስራኤል የምዕራባውያን አጋሮች ይህንን ድርጊት የማስቆም “ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተፈጸሙት ወንጀሎች መካከልም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋውያን መገደላቸው፣ የግዳጅ መፈናቀልና የምግብ እጥረት፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች እና የሲቪል መሠረተ ልማቶች መውደማቸው ፍልስጤማውያንን ከጤና አገልግሎት፣ ከትምህርት እና ከሌሎች መሰረታዊ መብቶች እንዲገፈፉ መንሰዔ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የበትሴለም ዳይሬክተር የሆኑት ዩሊ ኖቫክ “እየተመለከትን ያለነው አንድን ቡድን ለማጥፋት ታስቦ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግልጽና ዓላማ ያለው ጥቃት ነው” ሲሉ ገልጸው፤ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
እስራኤል ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ በግዳጅ በማስወጣት በሌሎች አገሮች ለማስፈር እያደረገችው ያለውን ጥረት ብዙ ተቃውሞ ቢገጥመውም መንደሮች አፍርሳ ወደ ምድረ ባዳነት እንደቀየረችው ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዚህም ሺዎች መኖሪያ አልባ ሆኖ በረሃብ እየሰገፉ መሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “ግልጽ እንሁን፣ ዌስት ባንክን በሐይል መቆጣጠር ህገወጥ ነው። መቆም አለበት። በጋዛ አጠቃላይ ውድመት ልንታገስ አንችልም። መቆም አለበት” ብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በጋዛ ረሃብ የሚባል የለም፤ ስራችን ግን እንቀጥላለን” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ሐቁን አልካዱም። “በጋዛ በእርግጥም ረሃብ አለ” ሲሉ ትራምፕ ተናግሯል።