
ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/11/2017፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ፤ በአገራችን ያንዣበበው አደጋ ለመቀልበስ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍንና መጪው ምርጫ ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ ይሆን ዘንድ “በገዢው ፓርቲ ላይ ተገቢውን ጫና ለመፍጠር ለምናደርገው ትግል መራጩ ህዝብ የምናቀርበውን ጥሪ እንድትከታተለንና ከጎናችን እንድትቆም” በማለት ጥሪ አቅርቧል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (አፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) ጨምሮ ስምንት ፓርቲዎችን ያካተተው ኮክሱ ትናንት ሐምሌ 21/ 2017 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መራጩ ህዝብና በነጻና ገለልተኛ ተዋናዮች፤ በምርጫ ሂደቱ ላይ ያለውን እምነት የት እንዳደረሰው “በዓለም አደባባይ የተሰጣ ሃቅ ነው” ብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ በመግለጫው፤ “ምርጫ ቦርድ እንደተቋም ያለበት የነጻና ገለልተኝነት ጥያቄና የገዢው ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚነት ክስ በዕድሜው እየቀረፈው የመጣው ችግር ሣይሆን እየተባባሰ የመጣ ነው” ሲልም አክሏል። “ይባስ በሚያስብል ለምርጫው ከዓመት ያነሰ ጊዜ በቀረበት ጊዜ ከገማሽ በላይ (60 ከመቶ) አባላቱ በአዲስ ተሹመዋል” ሲሉም ወቅሷል።
በተጨማሪም ይህን በሚያጠናክር መልክ የምርጫ ህግ ለማሻሻል በሚል ቦርዱ እንደ ነጻ የዴምክራሲ ተቋም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የባለድርሻ አካላትን የማሻሻያና የትኩረት ነጥቦች ከማገናዘብ፣ ከተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታው አንጻር መመመዘን ይልቅ “በተቃራኒው ተገኝቷል” ሲልም ከሷል።
ፓርቲዎቹ፤ ከመጪው ምርጫ በፊት የቦርዱ “ሀጋዊ የአሰራርና ተቋማዊ ችግር እስካልተፈታ ድረስ ለምርጫ መዘጋጀት የሚለው ሀሳብ ትርጉም አልባ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በእነዚህ ሁኔታዎቸ “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊኖር አይችልም” ያለው መግለጫው፤ “እውነተኛ ሪፎርም ከሌለ በኢትዮጵያ ተኣማኒ፣ አካታች፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊኖር አይችልም” ብሏል።