አልሸባብ በሶማሊያ ስትራቴጂክ ቦታ መቆጣጠሩ አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 21/11/2017፡ አልሸባብ ከ11 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ጦር እንዲለቅ የተደረገውን እና በሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት ስር የነበረችውን ማሃስ ከተማ ዳግም በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱ ገልጿል።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ዛሬ ማለዳ ባወጣው ዘገባ መሠረት በማዕከላዊ ሶማሊያ ሂራን ክልል ውስጥ የምትገኘው ማሃስ ትናንት እሁድ ከባድ ውጊያ ተካሂዶባታል። አልሸባብ በከተማዋ ላይ ጥቃት የፈጸመው ተቀጣጣይ ፈንጂ በጫኑ መኮኖች በመታገዝ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር በአካባቢው ስላለው ግጭት ባወጣው አጭር መግለጫ የአካባቢ እና የመንግሥት ኃይሎች በርካታ የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደላቸውን ገልጿል። ነገር ግን ሚኒስቴሩ ምን ያህል ታጣቂዎች እንደተገደሉ የገለፀው ነገር የለም። የአከካባቢው ነዋሪዎች በአልሸባብ እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በነበረው ውጊያ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ትናንት በማዕከላዊ ሶማሊያ ቁልፍ በሆነችው ማሃስ ከተማን በያዘ ጊዜ 63 የሶማሊያ ወታደሮችን መግደሉን እና 84 ሰዎችን ማቁሰሉን አስታውቋል። የቡድኑ ልሳን የሆነው ‘ራዲዮ አንዳሉስ’ እንደዘገበው በሂራን ክልል በማሃስ ከተማ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በከተማዋ እና በአካባቢው ከመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት “በዋና ወታደራዊ ካምፕ ላይ ያነጣጠረ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፈንድቷል” ብሏል።
‘ዘ ዴይሊ ሶማሊያ’ በኤክስ ገፁ ላይ እንደዘገበው ከተማዋን ሲከላከሉ የነበሩት የማአዊስሊ ሚሊሻዎች ከተማዋን ለቅቀው ለመውጣት ተገድደዋል።
የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምላሽ ባይሰጡም የአገሪቱ መከላከያ ግን ከከተማዋ አቅራቢያ ባለች ከተማ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት መመከቱን ተናግሯል።
የማህስ ከተማ በአልሸባብ እጅ መውደቅ የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ስትራቴጂካዊ ወሳኝ ቦታን ለማስጠበቅ ያደረገውን ከባድ ውድቀት ያሳያል ተብሏል። ይህም ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ያለውን ተአማኒነት የሚያሳጣ እና በወታደራዊ ዝግጁነቱ እና ቅንጅት ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደሚፈጥርም ተገልፃል።
እንዲሁም በአልሸባብ ፈጣን እና የተቀናጀ ኦፕሬሽን ቡድኑ በማዕከላዊ ሶማሊያ እያደገ ያለውን ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ አቅም አጉልቶ እንደሚያሳይ ተመላክቷል።
አልሸባብ መሃስን ሲቆጣጠር የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በአዲስ አበባ ይገኛሉ። ፕሬዝዳንት መሐሙድ በሁለተኛው የዓለም ስርዓተ ምግብ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ትላንት መክሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በ X ገፃቸው ባጋሩት መልእክት ሶማሊያና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በማስታወስ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ መስማማታቸው ገልጿል።