ኢትዮጵያ
“በቢሾፍቱ የሚገኝ ቤቴ በፖሊስ ታሸገ” ሲሉ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ገለፁ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 11/11/2017፡ ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው፣ “የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልያዙ ፖሊሶች” ቢሸፍቱ ከተማ ከሚገኘውና ከአገር ከመውጣታቸው በፊት ለ10 ዓመት ከኖሩበት ቤት በ10 ቀናት ውስጥ እቃቸውን እንዲያወጡ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ቤቱ ላይ ለጥፈው እንደሄዱ ለመገናኛ ብዙኀን ባሠራጩት መረጃ አስታውቀዋል።
ደብዳቤው፣ ቤቱ “ለማኅበራዊ ፖሊስ” አገልግሎት እንደሚፈለግ የሚገልጽ መሆኑን አቶ ልደቱ ገልጸዋል። በ10 ቀናት ውስጥ ቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ካልወጣ፣ ፖሊስ እርምጃ እንደሚወስድ በደብዳቤው ላይ ማስጠንቀቁንም ጠቅሰዋል።
የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ የያዘውን ደብዳቤ የጻፈው፣ በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የሆራ አርሰዴ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እንደኾነም ልደቱ ገልጸዋል።