
ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/1/2017፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በቪዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የየትኛውም ሀገር ዜጎች ከተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካለፉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው የዓመቱን ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት እና ሳምንታዊ ክንውኖችን አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በቀጣዮቹ ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በብቃት ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባዔ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 እንደሚካሄድ ተገልፀዋል፡፡ እንዲሁም እስከ 25 ሺህ ተሳታፊዎች ይስተናገዱበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በጳጉሜን ወር እንደሚስተናገድ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ጉባዔዎቹን ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ለማስተናገድና ተሞክሮዎቿን ለማካፈል በዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ሊከተሉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ በተመለከተ መልዕክት ያስተላለፉት ቃል አቀባዩ፤ በትምህርት እና በጉብኝት ቪዛ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሰጣቸውን ጊዜ እንዳያሳልፉ አስገንዝበዋል።
ቀነ ገደቡን የሚያሳልፉ አካላት በተደረገው የህግ ማሻሻያ መሰረት ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስረድተዋል።
በቪዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የየትኛውም ሀገር ዜጎችም ከተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካለፉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የገለጹት አምባሳደር ነብያት፤ ቅጣቱ ህጉን ተላልፈው የሚገኙ የኢትዮጵያ መኖሪያ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ያካትታል ብለዋል።