
ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/1/2017፡ ይካሄዳል የተባለው ድርድር መንግሥትን፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ቡድኖችን፣ እና በኦሮሞ ፖለቲካ የሚሳተፉ ሌሎች ኃይሎችን ያካተተ እንደሆነ ዞብል ፖስት የተሰኘ መፅሄት ዘግቧል።
በመንግሥት እና በኦሮሞ የታጠቁና ያልታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይደረጋል የተባለውን ሁሉን አቀፍ ድርድር በተመለከተ፣ የአውሮፓ ሕብረት የአመቻችነት እና የአደራዳሪነት ሚናን እንደሚጫወት መረጃ ያ
አሳይቷል።
የጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ መንግሥት እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከየአቅጣጫው መነሳታቸው ተከትሎ፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይደረጋል የተባለውን ድርድር ዐቢይ አህመድ የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞቻቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ታሳቢ ሳያደርጉ አልቀረም ተብሎ ይገመታል።
ሁሉን አቀፍ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ድርድር ይደረጋል ከተባለባቸው ምክንያቶች አንዱ “የኦሮሞ አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል” በሚል ሲሆን፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን በማግባባት ላይ የሚገኙት አቶ አባዱላ ገመዳ እና አቶ ግርማ ብሩ “ድርድሩ የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞችን እና የውጭ ኃይሎችን በጋራ መታገል የሚል ውጤት እንዲኖረው ይጠበቃል” የሚል አቋም እንዳላቸው፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመፅሄቱ አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም በዐቢይ አህመድ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በተከታታይ ለሁለት ጊዜ በታንዛኒያ ድርድር ተደርጎ ሳይሳካ መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን በጃል መሮ የሚመራው ኦነግ ለዚህ ጥሪ ምላሽ አልሰጠም ተብሏል።