
ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/1/2017፡ “የትግራይ ህዝብም ሆነ የአመራሩ ፍላጎት እና ተስፋ የቆዩም ሆኑ አዳዲስ ችግሮችና ልዩነቶች ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀራረብ በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸው የሚል ነው” ብለዋል ህወሓት ባወጣው መግለጫ፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የሀይማኖት አባቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች “ትግራይ ወደ ግጭት፣ ጦርነት እንዳይገባ ስራችሁን አሁን ጀምሩ፤ ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም” ሲሉ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ህወሓት የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ማሳሰቢያ አስመልክቶ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ህዝብ ካሳና መልሶ ግንባታ እንጂ በደልና የጦርነት ማስፈራሪያ የሚገባው አይደለም” ብሏል።
የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ ህወሓትና የትግራይ የጸጥታ አካላት ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ምንም ዓይነት ዝግጅት እንደሌላቸው ለማረጋገጥ የሀይማኖት አባቶች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች መሬት ላይ በመውረድ እውነታውን ማየትና መታዘብ ይችላሉ” ሲል አስታውቋል።
እንዲሁም የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጄነራል ታደሰ ወረደ “በትግራይ በኩል ምንም አይነት ትንኮሳና ጦርነት አይኖርም” ብለዋል፡፡
” በተሳሳተ ድምዳሜና ውሳኔ በትግራይ ላይ ጦርነት እንዳይጀመር ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ያሉት ጄነራል ታደሰ “የሰማእታትን መታሰቢያና የአሉላ ዘመቻን ድል ስናከብር የጦርነትን በጎነት እየሰበክን አይደለም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ ቀዳሚ ተግባራችን ነው በማለትም አሳስበዋል።