አፍሪካፖለቲካ

የጅምላ መቃብሮች ተገኙ

ዓለም የረሳው ጉዳይ

 

ኢትዮ ሞኒተር: 16/10/2017: ትንታኔ ዜና

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ዋዛ ሁለት ዓመት አለፈው። በዚህ ሁለት ዓመት “ያልተነገረ እንጂ ያልተፈፀመ ነገር የለም” ይላሉ  የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች። የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት በአፍሪካ ስለሆነ እንጂ ሌላ ዓለም ውስጥ ቢሆን ብዙ በተባለለት ነበር የሚሉም አሉ። የዩክሬን ጉዳይ፣ የጋዛ ሁኔታ ዓለም ጦርነቱ ማስቆም ባትችል ብዙ ርቀት ሂዳበታለች። በጋዛ ጉዳይ ኔታኒያሁ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ በዩክሬን ጉዳይ ፑቲን ከቡድን 7 እንዲገለሉ ተደርጓል። አሁን ደግሞ ስለ ኢራን ብዙ እየተባለ ይገኛል።
ሱዳን ግን አፍሪካዊ ናትና ያን ያህል ትኩረት አልተሰጣትም። እኛም ይህ አለም የረሳው ግን ደግሞ ከፍተኛ ወንጀል እየተፈፀመበት ያለው የጎረቤታችን ጉዳይ እንድናነሳ ወደድን። አብራችሁን ከቆያችሁ የሚባክኑ ጊዝያት እንደማይኖራችሁ በመተማመን ነው።

የዑመር አልበሽር መንግስት ከ30 ዓመታት በኃላ እ.አ.አ. በ2019 በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገደ በኃላ ሱዳናዊያን ያን ያህል የተረጋጋ ህይወት መርቷል ማለት አያስደፍርም። መፈንቅለ መንግስት አድርጎ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሐይል እርስ በርሱ በፈጠረው የስልጣን ሹኩቻ ሱዳኖች “የዳቦ ዋጋ ተወዶብናል” ብሎ ካመፁበት የአልበሽር ስርዓት የባሰ ነገር ይመጣብናል ብሎ አላሰቡትም። ሰራዊቱ ለሁለት ተከፍሎ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገባ። ይህ የሆነው ከሁለት ዓመታት በፊት ሚያዝያ 2023 ነበር። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ሱዳናዊያን በማያቋርጥ ጦርነት፣ ግፍ  በተሞላበት የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በሚዘገንን የፆታዊ ጥቃት ውስጥ፣ በስደትና ረሃብ ውስጥ ይገኛሉ። 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን 150 ሺ ሱዳናዊያን በዚህ ጦርነት ምክንያት ህይወታቸው አጥቷል። 12 ሚሊዮን የሱዳን ዜጎች በአገር ውስጥና ወደ ውጭ አገር ተፈናቅሏል፤ ተሰዷልም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በቡድን ተደፍሯል፤ ቤቶችና መሰረተ ልማቶች ወድሟል።
አሁን እየወጡ ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተነሳው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይል/RSF ሆን ብሎ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየፈፀመ እንደሆነ ነው። በጦርነት ወቅት ልያጋጥም የሚችል የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚጠበቅ ቢሆንም በጄነራል መሓመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው RSF ግን ሰብአዊ ቀውሶች እና ውድመቶች እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ነው። በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይሉ የተፈፀሙ የጅምላ መቃብሮች፣ የቡድን ፆታዊ ጥቃቶች፣ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመቶች በመረጃ እየወጡ ይገኛሉ። ጥፋቱ በውጭ ሐይል ቅጥረኞችም ጭምር የታገዘ መሆኑ ደግሞ ከሚገመተው በላይ አድርጎታል። ሰሙኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የፈጣን ድጋፍ ሃይሎች በሱዳን በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችን በቅጥረኛነት በመላክ እና ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በመመልመሉ በመላ ሀገሪቱ በሱዳናውያን ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና አስገድዶ መድፈሮች ተከስተዋል።
ሐይሉ ባደረገው ከፍተኛ ኦፕሬሽን በሱዳን የሚገኙ በርካታ ሆስፒታሎችን እንደ አል-በራሃ ሆስፒታል፣ አህመድ ጋሲም ሆስፒታል፣ ካርቱም ሆስፒታል፣ ዳር አል-አትባ ሆስፒታል እና የምስራቅ ናይል ሆስፒታል ባሉ በርካታ ሆስፒታሎች ላይ በማተኮር ሆን ብለው በሱዳን የሚገኙ በርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶችን አውድሟል ይላል።
በተጨማሪም ለሱዳን ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ጠቃሚ ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ፋብሪካዎችን ወድመዋል። የሱዳን ብሄራዊ ሙዚየም እና ሌሎች በርካታ የሱዳን ጠቃሚ ቅርሶች የሚገኙባቸው ሙዚየሞች በካርቱም እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘርፈዋል፣ ወድመዋል። ይህም ሆን ተብሎ የሱዳንን ቅርስ እና ታሪክ የማጥፋት ተግባር ነው ይላል መረጃው። የኤሌክትሪክ ሐይል እና ባንኮች የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች በድጋፍ ሰጪው ሐይል ወድሟል።
በአልጃዚራህ ዋድ አል ኑራ መንደር በተፈፀሙ በርካታ ጥቃቶች፣ በዳርፉር እና በኮርዶፋን ግዛቶች በተፈፀሙ ጅምላ ጭፍጨፋዎች እንዲሁም በናሁድ ከተማ የጅምላ ግድያ እንደተፈፀመም መረጃው አሳይቷል። እራሱን የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይል ብሎ የሰየመው ሚሊሻ ሆን ብሎ የሱዳን ዜጎችን ንብረት በመዝረፍ ቤታቸውን እንዳወደመውም ይገልፃል። ይህ የሆነው ሱዳንን እገዛለሁ ብሎ እየታገለ ያለው ሐይል መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን አስገራሚ ያደርጓል ይላሉ አንዳንድ ፀሐፊዎች። 
የድጋፍ ሰጪ ሐይል በተቆጣጠራቸው የገጠርም የከተማም አከባቢዎች የማይፈፀሙ ግፎች እንደሌሉ የአይን እማኞች ይናገራሉ። ሚሊሻዎቹ በርካታ ዜጎችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በማሰቃየት እና በእርሻ መንደር በእድሜ የገፉ ሼኮችን እና እናቶች ሳይቀሩ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ይገድላሉ ይደፈራሉም። በራሱ በአማፂ ቡድኑ የሚለቀቁት ቪድዮዎችና ፎቶዎች እንደሚያሳዩም  እነዚህን ጥሰቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩና የተረጋገጡ ናቸው።
የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይሉ በተለያሉ አገራትና ቡድኖች የሚደገፍ መሆኑ የሱዳኖች ግፍ ጭካኔ የተሞላው እንዲሆን አድርጎታል። የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት እንደሚለው ፈጣን ደራሽ ሐይሉ እንደ አገር በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ እንደሚደገፍ ነው። የሱዳኑ መንግስት ይህ የውጭ ሐይሎች ድጋፍ በተደጋጋሚ የገለፀው ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት እንዲታይም መጠየቁ ይታወሳል። በዳርፉር ኤል ፋሻር ለተፈፀመው “ጄኖሳይድ” ብሎ የጠራውን የጅምላ ጭፍጨፋም የኢሚሬትስ እጇ እንዳለበት ተገልፆ ነበር። ከኢሚሬትስ በተጨማሪ ቻድና በሊብያ ኮማንደር ካሊፋ ሃፍታር የሚመራ ቡድን ለRSF እየደገፈ እንደሆነ ይገለፃል። በጄነራል አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ሰራዊት የድጋፍ ሰጪ ሐይሉ በሊብያው ካሊፋ ሃፍታር ቡድን ታግዞ የሱዳን፣ ግብፅና ሊብያ ድንበር የሆነው የሶስት መአዝን ስትራቴጂክ ቦታ መቆጣጠሩን ከሁለት ሳምንታት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል። ይህ ደግሞ የሱዳን ሉአላዊነትን መድፈር አድርጎ እንደሚቆጥረው ገልፆ ነበር።
የRSF ሐይል በውጭ አገራት ይደገፋል እንደሚባል ሁሉ የሱዳን ሰራዊትም ከግብፅና ኤርትራ መንግስታት እንደሚደገፍ ነው የሚገለፀው። ይህ የውጭ ሐይሎች እጅ ያለበት የሱዳን ግጭት ከከፋ ወደ ባሰ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ነው እየተገለፀ ያለው።
ረሃብ፣ በሽታ እና ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። በዚህም ህፃናትና እናቶች በከፍተኛ እየተጎዱ እንደሆነ ይገለፃል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው በሱዳን እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 30 ሚሊዮን ሰዎች ግማሹን ህፃናት ናቸው። እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት ከተፈናቀሉት 12 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ግማሹን ህፃናት ይሸፍናሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
የህፃናት ድርጅት ዩኒሴፍ እንደሚለው ህፃናት ማግኘት ከሚገባቸው እርዳታ 3% ብቻ ነው እየተሸፈነ ያለው። ይህ ለመሸፈን የ88 ሚሊዮን ዶላር ክፍተት እንዳጋጠመው የገለፀው ድርጅቱ ከቤተሰቦቻቸው የተነጠሉ ህጻናት ለከፍተኛ እንግልት፣ ብዝበዛ እና ለአሰቃቂ አደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ ሲል የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።


በጦርነቱ በተመሰቃቀለችው ሱዳን በሽታ በህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። የኮሌራ ወረርሽኝ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የሱዳን የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ከ80,000 በላይ ሰዎች በኮሌራ ሲያዙ ከ2,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ዘግቧል። ከእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ወደ 7,300 የሚጠጉ እና ከ 230 በላይ የሚሆኑት የሞቱት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው ተብሏል።
በአለም ጤና ድርጅት እና በዩኒሴፍ የተደገፈ የ10 ቀን ኮሌራ ክትባት ዘመቻ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የሱዳን ህፃናት ግን ከሞት አልታደጋቸውም።
ከ2,200 በላይ በኩፊኝ በሽታ ሲያዙ አምስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። ከነዚህም ከ60% በላይ የሚሆኑት ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።
ከቅርብ ጊዝያት ወዲህ በዳርፉር ግዛት እየተፈፀመ ያለውን ሰብአዊ እርዳታ እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ብዙዎች በረሃብና በበሽታ እንዲያልቁ እያደረጋቸው ነው ተብሏል። የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ዳርፉር የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ የድጋፍ ሰጪ ሐይሉ የኤል ፋሸርን ከበባ እንድያቁም አሳስቧል። እንዲሁም እርዳታ ይዞው በሚጓዙ ተሸከርካሪዎችና የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሱዳን ሰሜን ዳርፉር ሰብአዊ እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ በነበረው ኮንቮይ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት በፅኑ አውግዞ እርዳታውን በአስተማማኝ መልኩ ለማድረስ ኤል ፋሸርን ከበባ እንዲያቆም የፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎችን ጠይቋል።
ምክር ቤቱ በጋዜጣዊ መግለጫው፣ በሰኔ 2 በአል ኮማ አቅራቢያ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዟል፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና ዩኒሴፍ በጋራ ያሰማሩት እንደሆነ የተነገረለት ኮንቮይ  በመመታቱ የአምስት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ህይወት ቀጥፏል። በጥቃቱ  የህይወት አድን እቃዎችን የያዙ በርካታ የጭነት መኪናዎችም ተቃጥለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የእውነታ መርማሪ ኮሚቴ በሱዳን ሰብአዊ እርዳታ እንደ ጦር መሳሪያ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል።

ከሱዳን ጦር ጋር ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለት የዳርፉር ታጣቂ ቡድን ከሚያዝያ 2024 ጀምሮ የተከበበችውን የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል ፋሸርን ለመሸሽ የመኮሩ 100 ሰዎች በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይሉ ተጠልፏል ሲል ከሰዋል።
በሚኒ ሚናዊ የሚመራው የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ የሰሜን ዳርፉር ባለስልጣን ሞሃመድ አደም ኮሽ RSF ሰላማዊ ሰዎችን በመጥለፍ ከኤል ፋሸር በስተምስራቅ በሚገኝ ተቋም ውስጥ አስሮአቸዋል ብሏል።
የሚታገቱ ሰዎች  “ጦርነቱን ለማቀጣጠል” ለግዳጅ ምልመላ ይጠቀምባቸው ነበር ሲሉ ኮሽ ለሱዳን ትሪቡን ተናግሯል።
የአለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ተሟጓች ድርጅት አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል መረጃን ዋቢ አድርጎ አልጄዚራ እንደዘገበው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይሉ ፆታዊ ጥቃትን እንደጦር መሣሪያ እየተጠቀመበት እንደሆነ ነው። ታጣቂ ሐይሉ “በመላ አገሪቱ መጠነ ሰፊ ፆታዊ ጥቃቶች ሰብአዊ ውርደት፣ ቦታዎች ለመቆጣጠርና ለመፈናቀል እየተጠቀመበት ነው” ብሏል አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል። እንዲሁም “የRSF ግፍ የቡድን ፆታዊ ጥቃት፣ ጠለፋ፣ ፆታዊ ባርነት ያካትታል፤ ይህ ደግሞ የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ነወ” ብሏል አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል።
ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው በኦምዱርማን በታጣቂ ሐይሉ የተገደሉ የጅምላ 465 የጅምላ መቃብሮች ተገኝቷል። እንደዚህ ዓይነት ጅምላ መቃብሮች በተለይ በዳርፉር ኤል ፋሻርና ኮርዶፋን በብዛት ሊገኙ እንደሚችሉም ዘገባው ይጠቁማል።
አንዳንዶች የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያደረገው ጥረት ውሱን ነው በማለት ይወቅሳሉ። ከዚህ በፊት አሜሪካ በባይደን አስተዳደር እያለች ያደረገችው ሙኮራ ተጠቃሽ ነው። በወቅቱ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ተሳታፊ ነበሩ። ይሁን እንጂ የሱዳኑ ሉአላዊ ምክር ቤት ለRSF ድጋፍ የምታደርገውን ኢሚሬትስ ያለችበት ድርድር አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩ በእንጥልጥል እንዲቀር ሆኗል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሱዳን ጉዳይ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ እንደተጣለ እቃ ሆናል። ሱዳናዊያን ግን አሁንም አገራቸው የምድር ሲኦል ሆናችባቸው በሺዎች እያለቁ እና እየተሰደዱ ናቸው።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates