
ኢትዮ ሞኒተር፡ 13/10/2017፡ በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ “አምስተኛ ክረምት በሸራ ይብቃን” በሚል መሪ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ ለሶስተኛ ቀን ዛሬ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም እየተካሄደ ይገኛል።
ሰልማዊ ሰልፉ በትግራይ ጦርነት ምክንያት የተፈናቆሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ የተጠራ ነው። በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውሳኔ መሰረት የመንግስት ሠራተኞች ስራቸውን በማቆም በሰልፉ ታደመዋል። እንዲሁም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ተማሪዎችም ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። በተመሳሳይ የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ለሰልፉ ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ በከተማዋ ሮማናት አደባባይ እየተካሄደ ባለው ሰልፍ የሃይማኖት አባቶችና ቸከታዮቻቸው ተሳትፏል። በመቐለ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የተካሄደው ሰልፉ ዛሬ የመርሃ ግብሩ የመጨረሻው ቀን ነው።
በሰልፉ የተገኙት የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ “የትግራይን ብሄራዊ ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ለማረጋገጥ ሁሉም ጥረት ይደረጋል” ብሏል። የተፈናቀሉ ዜጎች ለአምስተኛው ክረምት እንዳይሰቃዩ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግም አቶ አማኑኤል አረጋግጧል።
“ለ5ኛ ክረምት በመጠሊያ ይብቃ” የሚለውን የተፈናቃዮች ሰልፍ በሱዳንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚገኝበት ጄኔቫ ከተማም ዛሬ ተካሂዷል።