ፖለቲካ

የኢትዮ ሞኒተር ትንታኔ: የእስራኤል የድሮን መንጋ ብኢራን ሰማይ ላይ!

ኢትዮ ሞኒተር፡ 06/10/2017: “እስራኤል የምትፀፀትበትን የአጸፋ ምላሽ እናደርጋለን” የኢራን አብዮታዊ ዘብ

“የoperation rising lion/የአንበሳ መንሰራራት ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር።

ይህ የኢራንና እስራኤል መልልስ ነው። ኢራን በእስራኤል የደረሰባትን ያልታሰበ ዱብ ዕዳ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
ኢራን በእስራኤል ግዛት ላይ የምትሰነዝረው የአጸፋ ምላሽ ከባድ ሊሆን እንደሚችልም ነው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ያስጠነቀቀው።

ኢራን የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ የሀገሪቱ መሪ አያቶላ ሰይድ አሊ ካሚኒ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ማስጠንቀቂያውን አውጥቷል።

አያቶላ በመልዕክታቸው ኢራን የአጸፋ ምላሿ ከባድ እና “እስራኤልን የሚያጸጽት” ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ንግግር ተከትሎ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ለእስራኤል “አስከፊ” ምላሽ በመስጠት በፈጸመችው ጥቃት እንድትጸጸት ያደርጋል ማለቱን የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል አቦልቃሲም ሸካርቺ: ኢራን “ከባድ” አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጀነራሉ እስራኤል ሌሊቱን የፈጸመችው ጥቃት በአሜሪካ ድጋፍ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም “የእጃቸውን ያገኛሉ” ብለዋል። ኢራን ዝታ ዝም አላለችም። ከ100 በላይ ድሮኖች ወደ እስራኤል ልካለች። የእስራኤል ሰማይ ግን እን ኢራኑ ተበርግዶ አልጠበቀም። የኤስራኤልም የጎረቤት አገር ዮርዳኖስም የአየር ክልል የኢራን 100 ድሮኖች ውጦ እንዳስቀራቸው አልጄዚራ ዘግቧል።
“ኢራን ወደ እስራኤል ከ100 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን  (ድሮኖችን) አስወንጭፋለች” ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት IDF ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፊ ደፍሪን ገለጹ።

ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ  “ኢራን ወደ እስራኤል ግዛት የሚመጡ ወደ 100 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (UAVs) ብታስወነጭፍም  እነዚህን ድሮኖች ለመጥለፍ እየሰራን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።  በመግለጫው እነዚህ ከኢራን የተወነጨፉ ድሮኖች እስራኤል ለመድረስ ብዙ ሰዓታት እንደሚወስድባቸውም አስረድተዋል።
የእስራኤል ጦር በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች የኒውክሌር ኢላማዎችን ጨምሮ ከአስር በላይ የሚሆኑ ወታደራዊ ኢላማዎችን መምታቱን ይፋ ያደረገው ዛሬ ሌሊት ነው።

በዚህ ከባድ በተባለው ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እስራኤል ” ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ” ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ሲቪሊያን ይገኙበታል ብለዋል።

የእስራኤል ጠ/ሚ ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ‘ኦፕሬሽን ራይዚንግ ላየን’ (የሚያንሰራራ አንበሳ ዘመቻ) ሲሉ የጠሩት አካል እንደሚቀጥል ይፋ አድረጓል።
በተጨማሪም ኢራን ለእስራኤል የህልውና ስጋት መሆኗን ተናግረዋል።

ኢራን በምላሹ በቅርቡ አጸፋዊ የመልሶ ማጥቃት ልታደርስ እንደምትችል የገለጸች ስትሆን እስራኤል ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቧል።

እስራኤል ግን ዕላማው ወታደራዊ ተቋማት ላይ እንደሆነ ነው የምትገልፀው። እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት “የኢራን ጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ሰራዊት (IRGC) አዛዥ እንዲሁም የኢራን ድንገተኛ አደጋ ትዕዛዝ አዛዥ መገደላቸውን አረጋግጠዋል። የኢራን የመንግስት ሚዲያም “የአብዮታዊ ጥበቃው ዋና አዛዥ ሆሴይን ሳላሚ መገደላቸውን” ብቻ ዘግቧል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች እና ሳይንቲስቶች እንደተገደሉ ነው።
ሆሴይን ሳላሚ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ እኝዲሁም የአገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ ተገድለዋል። ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል። ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ የኒውክሌር ሳይንቲስት በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺም ተገድለዋል።
ይህ ከማንም ጊዜ ለኢራን ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል የተባለለት ጥቃት ከጀርባወ አሜሪካ እንደምትገኝበት ኢራን ትከሳለች።

ኢራን “አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት ደግፋለች ” ስትል የከሰሰች ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ግን አገራቸው እንዳልተሳተፈች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ እንደሚያውቁ፤ ነገር ግን አገራቸው እንዳልተሳተፈች ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል።

በርግጥ አሜሪካ ከእስራኤሉ ጥቃት ጀርባ እጅ እንዳለባት በአደባባይ ልትገልፅ አይጠበቅም። በቀጥታ ባትሳተፍም ለእስራኤል መረጃ በርብራ በምስጠት ግን ልትኖርበት እንደምትችል ተንታኞች እየገለፁ ነው። አሜሪካ ከቅርብ ጊዝያት ወዲህ በኒኩሌር ዙሪያ ከኢራን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ደጋግማ ስትጠይቅ ታይታለች። ይሁን እንጂ ኢራን በተዘዋዋሪ እንጂ በቀጥታ ስለኒኩሌር ጉዳይ አልደራደርም በማለት አሻፈረኝ ብላለች። ስለሆነም እስራኤል ኢራን ለመደብደብ አሜሪካ ተባብራ ልትሆን ትችላለች የሚሉ መላምቶች ተበራክቷል። አሜሪካ ግን ደጋግሜ ኤኔ የለሁበትም እያለች ትገኛለች።

የትላንትናው የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ ኢራናዊያንን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች የተለያዩ አስተያየቶች እየሰጡ ነው።
የ ኢራን ዜጎች እስራዔል በፈፀመችው ድብደባ ድንጋጤና ቁጣ የተቀላቀለበት አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ። ድንጋጤያቸውን ያመጣው ከጥቃት ይጠብቁናል ያሉዋቸውን በየቀኑ የኢራን ምድርና የአየር ክልል በዘመናዊ መሳሪያዎችና በስልጡን ወታደሮች እየተጠበቀ ነው እያሉ ሲፎክሩ የከረሙት የጦር አዛዦች ራሳቸውንና ሳይንቲስቶችንም ማዳን አቅቷቸው ሲገደሉ ማየታቸው እና ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ከእስራዔል ጥቃት ነፃ አለመሆኑን መረዳታቸው ሲሆን፣ በቁጣ እንዲሞሉ ያደረጋቸው ደግሞ በድብደባው የደረሰው ጉዳት መጠን ነው ተብሏል።
ፎቷቸው እየተለጠፈ ከራሽያ መጣ፣ ከቻይና ተገዛ፣ ራሷ ኢራን ሰራችው ሲባሉ የከረሙት የአየር መቃወሚያዎች የት ገብተው ነው በጥቅምት ወር ከመቶ በላይ ጥቃቶችን ሲፈፅሙና ዛሬ ደግሞ ከ200 በላይ ጀቶች ተሰማርተው በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተመላለሱ ከ330 በላይ ድብደባዎችን ሲፈፅሙ አንድም የእስራዔልን ጀት መተው መጣል ወይም አንዱንም የኒዩክሌር ሳይት ወይም ዋና ከተማዋን መከላከል ያቃታቸው? የሚለው የኢራን ዜጎች ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ማ/ሰብ ዓለም ጥያቄ ሆኗል።
የተለያዩ አገራትም ጥቃቱን እያወገዙትና ስጋታቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት የኢራን ሉዓላዊነት እና ደህንነት የሚያናጋ እና አለም አቀፍ ህግጋቶችን እና መመዘኛዎችን በግልፅ የሚጻረር ጥቃት በማለት አወግዞታል።

“ኢራን እና እስራኤል ውጥረትን ከሚያባብሱ ነገሮች እንዲቆጠቡ” ያሳሰበቸሸ ደግሞ ታላቋ ብራታኒያ ናት። የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር  በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረጉትን ጥቃቶች “አሳሳቢ ናቸው” ብለዋል።

“በቀጠናው ማንኛውም ግጭት እንዲባባስ መደረጉ ለማንም አይጠቅምም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር፣  “በመካከለኛው ምስራቅ መረጋጋት  ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፣ ውጥረቱን ለመቀነስ ከአጋሮቻችን ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል። አሁን ጊዜው የመረጋጋት እና ችግሩን በዲፕሎማሲ የመፍታት” ነው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ የስታርመርን “የተረጋጉ” ጥሪ በማስተጋባት፣ ኢራን እና እስራኤል ወደ ከፋ ግጭት መግባት “ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ከባድ ስጋት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“በመካከለኛው ምስራቅ ያለው መረጋጋት ለዓለም አቀፍ ደህንነት ወሳኝ ነው። ያለንበት አደገኛ ጊዜ በመሆኑ  ሁሉንም ወገኖች ራሳቸውን አደብ እንዲገዙ አሳስባለሁ” ሲሉ ላሚ አክለዋል።
አሁን እስራኤልና ኢራን ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል። እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት ሳትቋጭ አሁን ሌላ ጥቃት መፈፀሟ በረግጥም መካከለኛ ምስራቅ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስብል ይሆናል። ይሁን እንጂ የመካከለኛ ምስራቅ ቀውስ በቀጠናው ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ጦሱ ለመላው ዓለም እንደሚተርፍ ብዙዎች ይስማማሉ። የሁለቱም አገሮች ፍጥጫ ገና በአንድ ቀን እንኳ በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል እየተባለ ነው።

እስራኤል ኢራን ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 13 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ መረጃዎች ጠቁሟል።

ከ2020 በኋላ በቀን ውስጥ በዚህ ደረጃ ሲጨምር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 78 ዶላር ገብቷል።

አሁን ያለው ውጥረት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ መቆራረጥ እንዳይፈጥርም ተሰግቷል።

ተንታኞች ውጥረቱ ተባብሶ በዚሁ ከቀጠለ ሁኔታው ​​የዓለምን የኃይል ገበያ የበለጠ ሊያናጋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም የእስራኤልና የኢራን ውጥረት እንዲረጋጋ ብዙዎች እየተማፀኑ ነው።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates