
ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/10/17፡ህወሓት በየሳምንቱ ይፋ በሚያደርገው መልእክቱ “የፌዴራል መንግስት በምእራብ ትግራይ ታጣቂዎችን እያጠናከረ ነው” ሲል ከሷል፡፡ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሀት ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫው በምእራባዊ ትግራይ በመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ታጣቂዎች በደል መፈፀማቸውን ቀጥለውበታል ብሏል፡፡
ጨምሮም “እነዚህን ታጣቂዎች የፌዴራል መንግስቱ የማስወጣት ሀላፊነት ያለበት ቢሆንም በተለያየ መንገድ እንዲጠናከሩ እያደረገ ነው” በማለት ከሷል። ህወሓት በሽራሮ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ በየወሩ ከ250 እስከ 300 አዳዲስ ሰዎች ከምእራብ ትግራይ እየተፈናቀሉ እንደሚገቡም አስረድቷል፡፡
በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመተግበር ከመከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሀይሎችን ከትግራይ እንዲያስወጣና ተፈናቃዮችን ወደቤታቸው እንዲመልስ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ከሁለት ዓመታት በፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቆምም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እስካሁን መመለስ አልቻሉም። በዚህም ለአምስተኛ ክረምት በጊዝያዊ መጠሊያ እንዳያሳልፉ ሰግቷል።
ሰሙኑን “ፅላል” የተሰኘ የምዕራብ ትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ እንዳስታወቀው ከሰኔ 11 እስከ 13 በመቐለ እና ጄነቫ ከተሞች ከፍተኛ ህዝባዊ ሰልፍ ይደረጋል።
ህዝባዊ ሰልፉ “አምስተኛ ክረምት በመጠሊያ ይበቃል” የሚል መሪ ያለው ሲሆን በረሃብ እያለቁ ያሉት የትግራይ ተፈናቃዮች ከክረምት በፊት ወደቀያቸው እንዲመለሱ በኢትዮጵያ መንግስት ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።